እቃ ማጠብ
ትግስት መዝገቡ (ትኩስ ብስኩት)
Writing
እጄ እርጥብ… ሽቦዉ እርጥብ…. መጥበሻዉ እርጥብ… እጄ ሽቦዉን ጭብጥጥጥጥ አርጎ ይዟል … ሽቦዉ ደግሞ መጥበሻዉ ላይ ጥብቅቅቅቅቅ… መጥባሻዉ ደግሞ የሽሮዉን እራሪ ልክክክክ አርጎ ይዟል። ባለ በሌለ ሃይሌ እቧጥጠዋለሁ። አይለቅም። ሽሮዉ መጥበሻዉ ላይ አሮ ነዉ ወይስ መጥበሻዉ ሽሮዉ ላይ አሮ? ወይስ የኔ ጨጓራ በዚህ መጥበሻ ምክኒያት ያረረዉ?
ምን እንደገፋኝ ሳላውቅ ተስፈንጥሬ መጥበሻዉን አጠገቤ የነበረዉ የቆሻሻ መጣያ ጋርቤጄ ዉስጥ ጣልኩት። የሆነ የማላቀዉ የነፃነት ስሜት ወረረኝ። የሻይ ብርጭቆዬን ካላላቀዉ ሻዩ ጋር አንስቼ መጥበሻው ጋር ቀላቀልኩት። አሁንም ደስስስስ… ቀጠልኩ የሻይ ማንኪያ፣ የሾርባ ማንኪያ፣ ጭልፋ ፣ መብያ ሳህን፣ የዉሃ ብርጭቆ፣ የሻይ ማጥለያ፣ የሻይ በራድ….ሁሉንም ቆሻሻ መጣያ ዉስጥ ሞጀርኩት። ከላይ ወደታች እያየሁት ፈገግ አልኩ። ሳልደክም ቁና ቁና ያስተነፍሰኝ ጀመር ። እቃዉን ትቼዉ ወጣሁ።
ተገላገልኩ። እንዴ…. ምን በወጣኝ?
ከልጅነቴ ጀምሮ እቃ ማጠብ አልወድም። እቃ ላለማጠብ ከቤት ጠፍቼ አዉቃለሁ፣ እቃ ላለማጠብ ተገርፊያለሁ፣ ተግፍቻለሁ፣ ተሰድቢያለሁ። ግን ኑሮ የእናት ቤት አያልቅም እና አሁን እቃ በየቀኑ አጥባለሁ። አንዳንዴም በቀን ሁለቴ ላጥብ እችላለሁ… አያስቅም?
ጥላቻዬ ከእቃዉ አይደለም ጥላቻዬ እቃ ማጠብ ካለዉ metaphor ጋር ነዉ።
1ኛ የምጠላዉን ነገር ሳልወድ በግዴ በየቀኑ ማረጌ ነዉ። የተማርኩት ትምህርት፣ የምሰራዉ ሥራ፣ ያች ሁሌ የማዋራት የሥራ ባልደረባዬ ፣ የታክሲ ሰልፍ፣ ቲክቶክ ማየት፣ ነጭ ሽንኩርት መላጥ፣ ስልክ ማዉራት፣ ዘመድ መጠየቅ….. ሳልወድ በግዴ እየተንፏቀኩ አደርገዋለሁል። የማልፈልገዉን ነገር ተገድጄ ማድረጌ ደሞ ለዚህ ብኩን ህይወት ተገዢነቴን ያስታዉሰኛል። እኔ አርጊ የተባልኩትን አድራጊ እንጂ………..ቢሆንማ እንጀራ መሬት ላይ አንጥፌ በበላሁ… ቢሆንማ ነጭ ሽንንኩርት ከነልጣጩ በገመጥኩ ……
2ኛ ድግግሞሽ….. ትናንት ፈቅፍቄ ያጠብኩትን መጥበሻ ዛሬም መፈቅፈቄ….
ትናንት ያለቀስኩትን እምባ ዛሬም ማንባቴ… ከትናንት ወዲያ ያጠብኩትን ማንኪያ ዛሬም ማጠቤ ነገም ተንስቼ ዛሬ የሄድኩትን መንገድ መሄዴ… ልክ እጄ የሳህኑን ጠርዝ በየቀኑ እንደሚዞረዉ እኔም ያንን አደባባይ መዞሬ… መሬት ባራሷ ዛቢያም በፀሃይ ዙሪያም ትዞራለች.. አዙሪት የሆነ ኑሮ… ታጥቦ የማይጠራ ሁሌ የሚቆሽሽ ገላ… የማስበዉ ሃሳብ አንድ አይነት፣ የማጥበዉ እቃ አንድ አይነት፣ የምሰማዉ ዘፈን አንድ አይነት፣ የማየዉ ፊት ያዉ አንድ አይነት…. ምን ጥቅም? ማጠብ እና አለማጠብ ምን ሊቀይር? መልሶ ለሚቆሽሽ መልሶ ለሚዳክር….
3ኛ መጠበቅ… የእኔም የእቃዉም… እቃዉ ከነወጡ.. ከነአረረ ሽሮዉ ከነአልተማሰል ስኳሩ.. እንደጣልኩት እንዳስቀመጥኩት እኔ እስካጥበዉ ይጠብቃል… አሮ.. በስብሶ..እስከነትራፊዉ እኔን መጠበቅ… ካላጠብኩት አይታጠብ… እኔም ከነእድፌ እጠብቃለሁ የሆነ እግዛብሄር ወይ የሆነ ተለቅ ያለ ከኔ በብዙ የሚሻል ሰዉ እስኪያጥበኝ.. እስኪያነሳኝ…. ግን ምን ጥቅም?? መልሶ ለሚያበክተኝ…
4ኛ ከእቃም የእቃ ዉድ መኖሩ … የ22 ብር እንቁላል ነዉ የ10000 ብር መጥበሻም የሚጠብሰው የ2000 ብር መጥበሻም የሚጠብሰዉ… ጨዉ ጨዉ የሚል እንባ እና ቀይ ደም ነዉ የሚወጣዉ… ደሞ ከሰዉ ሰዉ መበላለጥ ደሞ ከማጥለያ ማጥለያ ማበላለጥ…..
ሳላስበዉ እያሰብኩ በረንዳዬ ላይ ብዙ ቆምኩ መሰለኝ በረደኝ በዛ ላይ እራበኝ። ገባሁ። የጣልኩትን እቃ በሙሉ አየሁት። ነጻነት ወደ ሽንፈት ተመለሰ.. ሳስቅ… እቃዉን ከጋርቤጁ ውስጥ አወጣሁት …..
እርቦኛል…. መብላት አለብኝ….
ሥራም አለኝ መሄድ አለብኝ…
ኑሮ አለኝ መኖር ያለብኝ…
About the contributor
Tikus Biskut is a writer and content creator.
